11/11/2025
ታማኝነቱን በመስእዋትነት ያስመሰከረው ቡቺ
(ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው)
ነገሩ እንዲህ ነው
በአዲስ አበባ ከተማ ነው፤ቃሊቲ አካባቢ፤ አንድ ለእናት አገራቸው በውትድርና ያገለገሉ አባት ከ15 ዓመታት በፊት ገደማ አንድ ቡችላ ወደ ቤተሰባቸው አምጥተው ያስተዋውቃሉ።
ቡቺ እስኪጎረምስ ድረስ ከቤተሰቡ ጋር በሳሎናቸው አድርገው እንደልጃቸው ተንከባክበው ያሳድጉታል። ታዲያ ቡቺ ምግቡን እንኳን ከአባትየው እና ከእናትዬው እጅ ካልሆነ ሌላ ከማንም እጅ ንክች አያደርግም ነበር።
ታማኙ የቤተሰቡ አባል ቡቺ ታዲያ ሲጎረምስ እና ውጭ ውጪውን ማማተር ሲጀምር ነፃነቱ ተሰጠው። ቡቺ ደስተኛ፣ ጤነኛ እና የቤሰቡን አባላት በሙሉ በፍቅር የሚያጫውት አባል ነበር።
ግቢውን ለፀጉረ ልውጥም ሆነ ለሌባ ሳያስደፍር ቤተሰቡን ሲያስከብር የኖረ የቤተሰቡ ውድ አባል ለአባትዬው ደግሞ ቁጥር አንድ ወዳጅ ነበር።
ውሾች በባህሪያቸው የመንጋ እንስሳት እንደመሆናቸው የመንጋውን መሪ በሚገባ ለይተው ያውቃሉ። ቡቺም አባባ የመንጋው መሪ መሆኑን የተረዳው ገና በልጅነቱ ነው።
ከአባትዬው በቀር ቡቺን ማንም እንደልቡ ሊያስር እና ሊፈታ አይችልም ነበር።
ቡቺ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ይህን ቤተሰብ የተቀላቀለ ሰሞን ሊከትበው የመጣውን ባለሞያ በጣም በማስቸገሩ ከታቢው "ድሮግባ" ሲል ስም አውጥቶለት በዛው ስም ሲጠራም ነው የቆየው።
አባባ ውጭ ውሎ ሲመጣ ቡቺዬዬ በር ስር ሆኖ ጠብቆ ሆዱን እና አንገቱ ስር እያሻሸ ሳያጫውተው ወደቤት አሳልፎ አያስገባውም ነበር። አባባም ቡቺን ማላፋት ሰለቸኝ ሲል ተሰምተው አያውቅም... በዚህ መልኩ ቡቺ ከቤተሰቡ ጋር ያለፉትን 15 ዓመታትን በፍቅር ዘለቀ።
ታዲያ ከሁለት ሳምንት በፊት ይህን ቤተሰብ ያልተጠበቀ ከባድ ሀዘን አጋጠመው።
የቤተሰቡ መሪ አባባ ባጋጠማቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ91 ዓመታቸው ወደዚህ ዓለም ላይመለሱ ለዘልአለሙ አንቀላፉ።
ይህ ሀዘን ታዲያ ለእናታችን እና ለአባባ ልጆች ብቻ አልነበረም የከበደው፤ ቡችዬም የመንጋው አለቃ አባባ ከእንግዲህ ተመልሶ ላይመጣ ከቤተሰቡ መለየቱን አውቆታል።
ሆዱ ነግሮታል፤ ቡችዬ አባባ የገባበትን ደጃፍ ካለመታከት እየተቁለጨለጨ ቢጠብቅም አባባን መልሶ ለማየት ግን አልቻለም።
የአባባ ህይወት ካለፈችባት ቀን አንስቶ ቡችዬ እህል በአፉ አልዞረም፣ ውሃም ለመጠጣት ፍቃደኛ ልሆነም።
ዘወትር የቤተሰቡን አባል ሲያይ ካለረፍት የሚወዘውዘው ጭራው እንኳን አደብ ገዝቷል።
የአባባ አስከሬን ከቤት ሲሸኝ እንኳን የመጣውን የሀዘን ተካፋይ አላስወጣ አላስገባ በማለቱ የቤቱ ልጆች በግድ አቅፈው ወደጓሮ እንዲወስዱት አስገድዶ ነበር።
ቡችዬ በአባባ ህልፈት ክፉኛ አዝኗል፣ ለሁለት ሳምንታት ያክል ምንም አይነት ምግብም ሆነ ውሃ በአፉ ሳይዞር ዘወትር አባባን ያገኝበት ከነበረው ደጃፍ ላይ በኃዘን እና በርሀብ አንጀቱ ታጥፎ ኩርምት ብሎ ተኝቷል።
የቡቺ ነገር ያሳሰባቸው የቤተሰቡ አባላት ቡቺን አስገድደው ሊያበሉትም ሆነ ሲያፅናኑት ቢሞክሩም ቡቺዬ አንጀቱ እንደታጠፈ ፍንክች አላለም።
አዎ ቡቺዬ ገና በለጋነቱ አምጥቶ ያሳደገውን አባባ ተለይቶ መኖር አልቻለም፤ ዘለዓለማዊ ታማኝነቱን እና ፍቅሩን አባባን እስከመቃብሩ በመከተል አረጋገጠ።
አባባ በሞት በተለየን በ15ኛ ቀኑ ቡቺዬ ለቤተሰቡ ሌላ ትዝታን ጥሎ አባባን ተከተለ፤ በሞቱ ዳግም እውነተኛ ታማኝነቱን አረጋገጠ!!!
ሕይወቱን በሙሉ በታማኝነት ሲጠብቅ በኖረበት ቤት ጓሮ ቡችዬ ተቀበረ።
ቡቺዬ ለቤተሰቡ ተጨማሪ የሐዘን ምክንያት ግን ደግሞ የታማኝነት እና የዘልአለማዊ ፍቅር ምሳሌ ሆኖ፣ ትዝታውን ጥሎ አለፈ።